--

Politics - ፖለቲካ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አንድ ጥያቄ አለኝ

(በበፍቃዱ ወንዳየሁ - ከዱራሜ ፣ ጥር 2007 ዓም )

...

ጠ/ሚ ደሳለኝ ኃ/ማርያም

(ይህን የእኔን ስሜት የማይጋሩና የማይመለከታቸው ብዙ ጓደኞች እንዳሉ አውቃለሁ፣ ነገር ግን የሚመለከተውና ሌላም ጥያቄ ያለው፤ በጎም ወይም ተግሳጽ እንዲሁም ሌላ ዓይነት አስተያየት እና ሀሳብ ቢያቀርብ ለመታረም ወይም ለመሻሻል ዝግጁ ነኝ፡፡ ከዚህ በታች ከቀረበው አጭር ወቅታዊ ጽሁፍ በተጨማሪ እራሱን በቻለ የፌስ-ቡክ ገጽ የሚቀርቡ፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ቁም ነገሮችን ለመለዋወጥ እንደመነሻ ሀሳብ ያገለግላሉ ብዬ የማስባቸው የተወሰኑ ጽሁፎችም አሉኝ ) ክቡር ጠቅላይ/ሚ እኔ ጥያቄ አለኝ !! "ጥያቄ ለመጠየቅ ምን ቤት ነህ ? ደግሞስ ማነህ ?" ይሉኛል ብዬ ተስፋ ሰልቆርጥና ሳልሰጋ፣ በዲሞክራሲያዊ መንግስት በምትተዳደር አንዲት ሀገር ውስጥ ጥያቄ ለመጠየቅ ዜጋ መሆን በቂ ነው ብዬ አስቤ ነው(በእኔ አስተሳሰብ እና እውቀት ደረጃ)፡፡ የማይቻል ከሆነ ደግሞ ማንኛውንም አይነት ትምህርት እና እርምት እቀበላለሁ፡፡ ጥያቄ መጠየቅና መደመጥ፣ ደግሞም መልስ ማግኘት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን አውቃለሁ፤ ግን ዝም ከማለት እና ታፍኖ ከመኖር ተንፍሼ ቢቀለኝ ይሻለኛል፡፡ -- አሉኝ ያልኮትን ጥያቄዎች በደምብ በማላውቀው ቋንቋ እንዳቀርብ እንዲፈቀድልኝ እስከዛሬ ድረስ ካለፈጣሪ በስተቀር ለማንም አሳይቼ በማላውቀው ትልቅ ትህትና እጠይቃለሁ !! ( የእኔን ጥያቄዎች ያቀርቡልኛል ብዬ የምጠብቃቸው ወዴት አንደደረሱ አላውቅም፤ የዋጣቸው ጅብ እስከሚጮህ ወይም እስከሚተፋቸው ልሞት አንድ ሀሙስ ብቻ/2007 ምርጫ ብቻ/ ቀረኝ )

1. በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች ክልል መንግስት ካሉ ብሔረሰቦች መካከል "ከምባታ" የሚባል ብሔረሰብ እንዳለ ያውቃሉ ? የመጀመሪያ ጥያቄዬ ይሄ ሲሆን እሄንን ማወቅ ይኑርቦት አይኑርቦት እኔ አላውቅም፡፡ … እኔ ከዚህ ማህበረሰብ ተወለጄ ያደግኩ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ ሌሎችን እንደሚያውቁት እኛንም ቢያውቁን ደስ ይለናል ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ በእርግጥ እርሶ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ስለነበሩ እና ከዚህ በፊት ደግሞ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ትልልቅ የመንግስስት ተቋማት ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ ስለሆነ "ረስቼአችኋለሁ" ካላሉን በስተቀር "አላውቃችሁም" እንደማይሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ክቡር ጠ/ሚ የእኔ ማህበረሰብ የልማት እጦት እና ቀውስ ውስጥ ያለ ነው፡፡ --- ስለዝህ በዚህ በልማታዊ መንግስት ቢጎበኝ እኔ በግሌ በጣም ነው ደስ የሚለኝ፤ ሌሎችም --ያለጥርጥር እንደዛው ፡፡ ፈጽሞ ከረሱን ደግሞ እንዲያስታውሱን ጥቂት ፍንጮችን እኔ እንድሰጥዎት ይፍቀዱልኝ --

• የተለያየ የጤና ችግር ሲያጋጥምዎ ከሚያማክሩአቸው ስፔሻልስት ዶክተሮች እና እግዚአብሄር በሰጣቸው ጥበብ ከሚያሳርፍዎ ዶክተሮች መካከል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ትልልቅ ሆስፒታሎች ውስጥ ለከባባድ የጤና ችግሮች መፍትሄ ከሚሰጡት መካከል የተወሰኑት የዚህ መኖሩ እንኳ የማይታወቀው ማህበረሰብ ፍሬዎች ናቸው፡፡

• የሚኖሩበት ቤተመቅደስ/ቤተ - መንግስት ሕንጻዎች ወይም ለተለያየ ሀገራዊ ጉዳይ እርስዎ ከሌሎች ጋር የሚታደሙባቸው ሕንጻዎች ያማሩባቸውን ቀለሞች ቀምመው ዓለም ያወቃቸውን ፣ ማወቅ ብቻ አይበቃም ብሎ ደግሞ የሸለማቸውን ጠቢባንስ አያውቋቸውም ? አንደነዚህ አይነት ሀገር የሚያስጠሩ ፍሬዎች ያፈራውን ማህበረሰብ እርስዎ ቢረሱት አይገርምም፣ ምክኒያቱም "አለን አለን" ስለማንል ጎረቤት እንኳን አያውቀንም፡፡ ---ኧረ ምን ጎረቤት እኛ እራሳችን ስድቡ ከብዶን ማንነታችንን አለማወቅ ጀምረናል !!

• ሌላው ደግሞ እርሶ ተወልደው ባደጉበት ማህበረሰብ እንኳን ጭምር ያለውን ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ለማስወገድ ቤታቸውን ብቻ ሳይሉ የታገሉ ጀግና እንስቶችን ማስታወሰ ከቻሉ እኛንም ያስታውሱናል፡፡

• ክቡር ጠ/ሚ ሌላም እንዲያስተውሱን --- መቼም ለተለያየ የሥራጉዳይ ወደ ውጭ ሀገራት ሲሄዱ የሚበሩበት ነገር ከምድር ከመነሳቱ በፊት እርሶ በመንገድ ላይ ችግር እንዳያጋጥምዎ ደህንነቱን ፈትሸው ከሚያረጋግጡት መካከል ቢያንስ ቢያንስ አንድ የእኔ ወንድም/አህት አለ/አለች፡፡ ደግሞም ከምድር ከተነሳም በኋላ ከቀናት በአንደኛው ቀን የእኔ ጓደኛ ወደሆነ ሀገር እርሶን ይዞ በርሯል … በእርግጠኝት !

• ደግሞም አንድ የሚገርም ማስታወሻ ልንገሮት፤ በሀገር ውስጥ ለተለያየ ሥራ ሲንቀሳቀሱ ከሚያጅቦት ጋርዶች መካከል ወይም በመንገድ ሲሄዱ በግራና በቀኝ ከሚቆሙት መካከል … ወይም ደግሞም እርሶና ቤተሰብዎ የሚያድሩበት ግቢ በሰላም እንዲያድር ነቅተው ከሚያድሩት መካከል አንድም የዚህ ማህበረሰብ ተወላጅ የለም ቢሉ ትዝብት ሊሆን ይችላል፡፡ …. እንደውም ብልጦችና ሚሰጥር ጠባቂዎች ስለሆንን ለንደዝህ ዓይነቱ ሥራ እንደሚመርጡን መገመት ይቻላል፡፡

• በውጭ ሀገራት የሀገራችንን ገጽታ መልካም አድርገው እንዲገነቡ ከላኳቸው አምባሳደሮች መካከል ቢያነስ ቢያንስ ሁለት ወይም ሶስት ይህ ማህበረሰብ ወልዶ ያሳደጋቸው ናቸው፤ በሀገር ውስጥ ግን የእኛ ገጽታ ከሁሉም የተበላሸ መሆኑን ስናስብ የምሬን ነው የምሎት በጣም ነው የሚከፋኝ፡፡

• ለሀገር ሰላምና ለሀገር ክብር የሀገሪቱ ሕዝብ በታገለበት ወቅት እኛም የብዙ ወንድሞቻችንን ነፍስ አዋጥተናል፡፡ … አንደውም ከክልሉ ብሄረሰቦች ለዚህ ከፍተኛውን ድርሻ ከሚወስዱት ጋር ልንሰለፍ አንችላለን፡፡ አኔ እንደማስታውሰው ብዙ ወንድሞችን፣ እናትና አባት፣ ወንድምና እህት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ደም እንባ አልቅሰው በተሳቢ እና በዖር መኪኖች ሲሸኙ በዓይኔ በብረቱ ተመልክቼአለሁ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ (አረ ሁሉም ማለት ይቻላል) እንዳልተመለሱ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ሀገር ስትቸገር እኛም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገን ጋራ የምንሰለፍ ስለሆንን በችግራችን ጊዜ ዝም አይበሉን !!

ከምባታ የሚባል ብሔረሰብ አለ !!

• በሀገር ጉዳይ/ልማት ወደኋላ የማንል መሆናችንን ካወቁልን ይወቁልን፡፡ …. በአሁኑ ወቅት አጅግ ወቅታዊ በሆነው እና በማንደራደርበት የሕዳሴያችን ግድብ ጉዳይ ሁላችንም የከምባታ ተወላጆች በደሞዝ ፣ በቦንድ እና በሎሎችም መንገዶች በደስታ በአንድ ልብ ተስማምተን ያለጭቅጭቅ የምንሳተፍ ስንሆን … በስራ አጥነት ምክኒያት ከሀገር ሲሰደዱ ከአውሬ፣ ከውኃ እና ከጨካኝ ባዕድ የተረፉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንኳን ደካማውን ወገናችንን ከሚረዱት ቀንሰው የሚችሉት የሚያደርጉ ስለመሆኑም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ይኖሮታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም በነፍስ ባለነው ባያስታዉሱን በበረሃ በጅምላ ሞተው ሬሳቸውን በመለሱልን ወንድሞቻችን ምክንያት እንኳን ይወቁን/ያስታውሱን፡፡

• ትላልቅ የትምህርት ተቋማት ባሉበት ዞኖች/ በሁሉም ማለት ይቻላል / ትውልድን እየቀረጹ ያሉ የዚህ የማይታወቅ ማህበረሰብ ወንድምና እህቶችን ልቆጥርሎት አልሞክርም፡፡ --- ምን አልባት እርሶ ልጆችዎን ኢትዮጵያ ውስጥ ላያስተምሩ ይችላሉ እንጅ ምርጥ በሚባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንኳን እውቅና አግኝተው የዜግነት ግዴታቸውን እየተወጡ የሚገኙ ኢንስትራክተሮች ፣ የዲፓርትመንት ሄዶች ፣ዶክተሮች እና ፕሮፌሰሮችን በስም ልጠቅስሎት እችላለሁ፡፡ … ነገር ግን አንዳንዶቹ የእነዚህ ወንድሞችና እህቶች ሌላ አካባቢ ሄደው ለመማር አቅም የሌላቸው በመሆናቸው ቤታቸው የሚቀሩ ናቸው፡፡

እሄን መዘባረቄ እራስን ከሌላው ከፍ አርጎ ለማየት የሚፈልግ ትምክህተኛና ጠባብ ማንነት ኖሮኝ ሳይሆን ስለተረሳን በጣም ከፍቶናልና እኛ የሀገራችን ታሪክ እንዲቀየር ከምናከብራቸውና ከመምንወዳቸው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር የድርሻችንን የምንወጣ "ከምባታ" የምንባል ማህበረሰቦች ነንና በእነዚህ በኩል አርግውም ቢሆን ያስታውሱን ብዬ ነው !!

2. ሌላው ጥያቄዬ ከሀገር ልማት ተጠቃሚ ለመሆን መስፈርቱ ምንድነው የሚል ነው ? መቼም የኢህአዴግን መንግስት መምረጥ ነው እንደማይሉኝ እርግጠኛ ነኝ …. ለዚህ ለዚህ ቀድሞውኑ የእርሶን ፓርቲ ፖሊሲ እንዲያስፈጽሙ ያስቀመጡልን አድር ባዮች የዞናችን ሕዝብ ኢህአዴግን ቢመርጥ ባይመርጥ ምንም እንደማይጨምር ምንም ደግሞ እንደማይቀንስ ነግረውን ተስፋ አስቆርጠውናል፡፡ … እንደውም ያለውም እንደሚወሰድብን … እየታሰበ ያለ ነገርም ካለ እንደሚቀለበስ አስጠንቅቀው አስፈራርተውናል፡፡ ይህን ጥያቄ የጠየኩት … አኔም ሆንኩ ወገኖቼ መስፈርቱን ብናውቅ በቴሌቪዢን መስኮት ብቻ የምናየውን ልማት የሚባለውን ነገር በአካል ለማየት እጅግ ስለናፈቅን/የሚበላ ይሁን የሚጠጣ ለማወቅም እጅግ ስለጓጓን የትኛውንም ድንጋይ ፈንቅለን ቅድመሁኔታውን ለማሟለት እንጥራለን ብዬ ነው !!

በክልሉ ውስጥ ከሚኖሩት ህዝቦች ሁሉ አስፓልት የሚባል ነገር የማያውቅ ሕዝብ ያለበት፣ የራሱን ወረዳዎች እርስ በእርስ ከሚያገናኙት ለአቅመ መንገድ ካልበቁ መንገዶች ውጭ ዞኑን ከአጎራበች ዞኖች ጋራ የሚያገናኝ ምንም አይነት ዋና የሚባል መንገድ የሌለው ዞን ሆኖ ፣ በጠባብ መሬት ላይ ተጠጋግቶ የሠፈረው ሕዝብ ተጨማሪ ሥራዎችን ሠርቶ ኑሮውን የሚያሻሽልበት አንድም ሰፊና ትልቅ የሚባል የመንግስት ተቋም ለስም እንኳን ሳይኖር፣ በአከባቢው ብዙ የተማረና ጠንካራ የሰው ኃይል እያለ፣ ዞኑን በደምብ የሚያስተዳደር አካል ሳያስቀምጡልን ምን ጎደላችሁ እንደማይሉን አስባለሁ ፡፡ (እነርሱን ስለልማት ስንጠይቃቸው ዶንግቾ ላይ ጤና ጣቢያ ሠርተናል ፣ High School አንድ ነበር ሕዳሴን ጨምረንላችኋል ፣ የውሃ እጥረት ነበር ጎቾ ላይ የከርሰምድር ውሃ ቆፍረናል …….. ይሉናል )

3. ሌላ ደግሞ መጠየቅ የሚፈለገው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዞናችን ካብኔቶች ማንንም ምንም ሳንነካ፣ " በሠላም ምድር ተሠብስባችሁ አትቀመጡ፣ አንድም ሁለትም ሶስትም ሆናችሁ አቧራኪያቶ አትጠጡ … ልማት የለም አትበሉ፣ እሄን ሁሉ አቧራ የምናነሳው እኮ አገሪቱን ለማልማት ላይ ታች ስንሯሯጥ ነው" እያሉ እያስፈራሩን ነው፡፡ ስለዚህ ከምድራችን፣ ከቀዬአችን ወዴት መሄድ እንዳለብን ይጠቁሙን ፡፡

4. እግዚአብሄርን የምንፈራና የተገባልንን ቃል በትዕግስት የምንጠብቅ በመሆናችንና ዝም ብለን ዝም ያልን ስለሆንን መረሳት አለብን ወይ? ….ወይስ መጯጯህ አለብን፡፡ ከምባታ የሚባል ብሄረሰብ አለ !!

የሚረዳን የለምና ኢህአዴግ ሆይ ከእኛ አትራቅ አንልም !! ችላ ካሉን ግን ለእኛ መዳን ከሌላ ስፍራ ይሆንልናል !!