--

Politics - ፖለቲካ

ጨለማን ጨለማ አይገልጠውም - ብርሃን እንጂ!

(መንቾ ከም፣ የካቲት 23 ቀን 2007 ዓ.ም)

...

ዶር. ማርቲን ሉተር ኪንግ

በተለያዩ ስፍራዎችና አጋጣሚዎች የፍትህ መጓደል፣ ለግል ጥቅም መስገብገብ ወይም የህዝብን አደራ መዘንጋት ሁኔታና ባህርይ የዚህ አገር ወይም የዚያ ተብሎ የሚጠቆም ሳይሆን የትም ሲከሰት ይታያል፡፡ ሰዎች ሁከትን በመጥላትና በተጠመዱባቸው ሌሎች ጉዳዮች ላይ አተኩረው፣ አንዳንዴ ባካባቢያቸው ስለሚደረገው ዝርክርክ አሰራርና ሙስና ተቃውሟቸውን ወዲያው ባለማሰማታቸው ሁሌም በፍትህ ስለተንበሸበሹ ወይም ግድ ስለሌላቸው ነው ብሎ ማሰብ ስንፍና ነው፡፡ አንድ ቀን ትዕግስታቸው ሲያልቅ ሊያደርሱት የሚችሉትን ጥፋትና አጸፋዊ ምላሽ ስግብግቦችና የሰውን ባህርይ አስተውለው የማይረዱ ጥቂት ሃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች አስቀድመው ላይገነዘቡት ይችላሉ፡፡ አያምጣው እንጂ፣ እነርሱ ግንዛበቤ ይጎድላቸዋል ማለት ጥፋቱን አይቀንሰውም፤ ወይም ጉዳቱን አያስቀረውም፡፡በዚህ ሁሉ፣ የሰዎችን ሀሳብ አክብሮ፣ ማንነታቸውን ሳይዘነጉና ሰው መሆናቸውን ተቀብሎ ከስህተት መታረምና የሚያከራክሩ ጉዳዮችን ማርገብ አስፈላጊ ነው፡፡

ጨለማን ጨለማ አይገልጠውም፤ ብርሃን እንጂ፡፡ ሰው እንደመሆናችን አስተሳሰባችንና ፍላጎታችን ይለያያል፤ ለነገሮችና ለችግሮች መፍትሄ የምንፈልግበትም መንገድ አንድ ዓይነት ባይሆን አይገርምም፡፡ የሚገርመው፣ "ሁሉም ሰው በኔ መንገድ ያስብ፣ ወይም ደግሞ ከኔ ውጪ የሌላው ሀሳብ ሁሉ ዋጋ የለውም" ማለት ስንጀምር ነው፡፡ ከሌሎች ሰዎች ሀሳብን እየተቀበልን ባለንበት በዚህ አጋጣሚ በከምባታ ጠምባሮ ዞን ሰሞኑን ጎልቶ ስለሚደመጠው “የልማት ይዳረሰን” ጥያቄ አንጻር እኔም የሚከተለውን እንድል ሁኔታው ገፋፍቶኛል፡፡

መቼስ አንድን ነገር ለመፍታት ወይም መፍትሄ ብሎ ሀሳብ ለመሰንዘር “ችግሩን መረዳት ግማሹን ያህል የመፍትሄ ፍለጋ መንገድ እንደመሄድ ይቆጠራል” ይባላልና ለዚያ መሰረታዊ በሚሆነው ጉዳይ ላይ ትንሽ ልበል፡፡ ወዲያ ወዲህ ከማለት ይልቅ ቀጥታ የችግሩ ቁልፍ ናቸው የሚባሉትን ጉዳዮች መጥቀስ አስፈላጊ ነው፡፡ ቀጥለው የተጠቀሱት ነገሮች ተደጋግመው የሚነሱ፣ ከአካባቢው አለመልማት ጋር ተሰናስለው የሚሄዱ እንደሆኑ የሚነገሩና በተለያዩ ውይይቶች ወቅት የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ናቸው፡፡ እነዚህም፣ “ተመካክሮ አለመስራት፣ ህዝቡን አንድ አድርጎ በማስተባበር ለልማት ማነሳሳት አለመቻል፣ በምንም ይሁን በምን ስልጣን ላይ ከተወጣ ያንን ለማቆየት ከመጣር ያለፈ በዚያ አንጻር ለአካባቢው ሊደረግ ስለሚገባው ቀና አመራርና ግንባታ ቸልተኛ መሆንና ከአቅም ማነስ ጋር በተያያዘ የሚከተለው ስግብግብነትና ግድየለሽነት” ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

የምንኖረው ለአጭር ጊዜ ነው፣ ይህን አጭር እድሜ ደግሞ ቢቻል ቀና ነገር ሰርተንበት ካልሆነም ደግሞ ለሰዎች የሚበጅ ነገር የሚፈጠርበትን መንገድ አመቻችተን ብናልፍ ትልቅ እድል ነው፡፡ እንደዚህ ለመሆን ደግሞ የትምህርት፣ የዘር፣ የሀብት ወይም ሌላ ልዩ የሆነ ችሎታን የሚጠይቅ ሳይሆን ቀናነትን ወይም መልካም ስብዕናን ከመላበስ የሚመነጭ ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ለአንድ አካባቢ መሪነት ሲታጩም ሆነ በስልጣን ሲያገለግሉ፣ አገልጋይ መሆናቸውን እርግፍ አድርገው ዘንግተው ራሳቸውን የሚያደላድሉ ሲሆኑ ማየት ባሁኑ ዘመን የተለመደ ነው፡፡ ቋንቋንና ዝምድናን ዋነኛ መሰረት አድርጎ በተዋቀረው የኢትዮያ ፌዴራላዊ አስተዳደር ስርዓትም አንዳንድ ጊዜ የራሳቸውን ህዝብና የገዛ ዘመዶቻቸውን እንዲያስተዳድሩ የሚመረጡ (የሚመደቡም ሆነ የሚሾሙ) ሰዎች የገዛ ራሳቸውን ማህበረሰብ ለሚጎዳ ዓላማ ሲሰለፉ እንደማየት የሚከብድ ነገር የለም፡፡

አንዳንዱ ሰው በዘመድ፣ ባጋጣሚ፣ ሰው ጠፍቶም ይሁን ይሄ ነው በማይባል ሌላ የራሱ ምክንያት ስልጣን ላይ ወጥቶ ሲገኝ ሁሉን የሚያውቅ፣ የነገር ሁሉ ፈጣሪና ሰሪ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡ ያዋቂን ምክር፣ ያባቶችን ሀሳብ፣ የሊቆችን ስላጤ፣ የድሃን ምርቃትና የነገውን ሀገር ተረካቢ ወጣት ጩሀት መናቅ ዕድገትን ሳይሆን የአስተሳሰብ አለመብሰልን ነው የሚያረጋግጠው፡፡ "ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣ አለዚያ ድንጋይ ነህና ትወረወራለህ" ተብሎ እሚተረተውም ይህን ለመግለጽ ነው፡፡

መመካከር ማንን ገደለ፤ "እየለማች፣ እያደገች ነው" በምትባለዋ በዚች ታለቅ ሀገር፤ በብዙ ድካምና ትግል ራሱን አስተምሮ፣ በየገደሉና ጥጋጥጉ ሳይቀር ዞሮ አገር ያቀናው የከምባታ ህዝብ፣ በዚህ "ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ራሱን ማሳደግ ይችላል፤ የአገሪቱንም ሀብት በተመጣጣኝ ይካፈላል" በተባለበት ስርዓት የበይ ተመልካች ለምን ይደረጋል? ቀድሞ መሰልጠንና ሌሎችን ማገዝ የበለጠ ያስከብራል እንጂ ለምንስ ችላ እየተባለ በረባው ባልረባው ሁሉ ምክንያት እየተፈለገለት በፌዴራልና በክልሉ መንግስት በኩል የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እድል ያጣል? ሌላው ቢቀር ለልዩ ወረዳዎች እንኳን ሳይቀር ኮንዶሚኒየም በሚገነባበት የደቡብ ክልል ላይ እውነት የከምባታ ጠምባሮ ዞን ምን ቢያጠፋ ነው ሁለት ብሎክ እንኳን የተነፈገው? ዩኒቨርሲቲ ለመክፈትስ ቢሆን ስሌቱ የሚጀምረው ዙሪያውን ለሌሎቹ እንዲዳረስ ከተደረገ በኋላ፣ "ባቅራቢያው አለ" እየተባለ የሚሆነው በየትኛው መስፈርት ነው? ይህን ያህል የኗሪ ብዛት፣ የተማረ ሰው ሃይል ብቃትና መጋቢ ትምህርት ቤቶች ወይም በክልሉ ቀድመው ከተመሰረቱት ዞኖች የትኞቹ በልጠውት ነው ለሚሉት ጥያቄዎች መቼም መልስ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡

ብዙ መናገሩ የሚያውቁትን መድገም፣ የተባለውንም ማብዛት ሊመስል ይችላል፡፡ እውነት ስለሆነ ግን አሁንም አስፈላጊ ሲሆን በስታትስቲክስ የተደገፈ መረጃ በማቅረብ፣ እየተደረገ ያለው ነገር ለብዙ ዘመናት አብረን የኖርነውን ባካባቢያችን ያሉ ዘመዶቻችንን ሁሉ የሚያስተዛዝብ እየሆነ መምጣቱን መግለጽ ግን የግድ ነው የሚሆነው፡፡

በደቡብ ክልል ያሉ ዞኖችም የከምባታ ጠምባሮ ዞን በክልሉ ካሉ ሌሎች ዞኖች ሁሉ ከእድገት እንደራቀና ማህበረሰቡ ከሚያደርገው አስተዋጽዖና ጥረት አንጻር ትኩረት እንደተነፈገው ባይክዱም፣ ይህን ችላ ያሉበትን ምክንያት ግን ከራሱ ከዞኑ መሪዎች ጋር የተያያዘ ችግር ነው በሚል ይከራከራሉ፡፡ ይሀውም፣ " በአንድ በኩል በራሱ በዞኑ ተወካዮች ድክመትና አላስፈላጊ ይሉኝታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በዞኑ ሰዎች ለስልጣን ከመስገብገብና ከአቅም ማነስ የተነሳ የሚገባቸውን እንኳን ለመጠየቅ በራስ የመተማመን ስለሚጎድላቸው" እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይህ አባባል የሁሉም ችግር ቁልፍ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች እንደሚስማሙ በተለያዩ አጋጣሚዎች የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም የሰማው ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሁኔታ እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል? እውነቱን ለመናገር፣ “መንግስት ሊሸፍን ባልቻለው ቀዳዳ ያሉትን ክፍተቶች ለመድፈን፣ የራቀውንም ወደሀገሩ እንዲያስብ ለማቀራረብ እናግዝ ሲባል”፣ ዘር እየተቆጠረ፣ ሰፈር እየተመነዘረ፡ ወረዳ እየተደረደረ፣ "አመለካከት" በአሉባልታ እየተሰፈረ፣ ከመደንበርና አንዱን ከሌላው በሀሜት እያጋጩ ከማራራቅ ወዲያ አመራሮቹ የረባ ስራ ሲሰሩ አይታዩም የሚሉ የአካባቢው ተወላጆች ብዙ ናቸው፡፡

ሌላው ቀርቶ፣ አብረን እንስራ ብቻ ሳይሆን፣ "ይህን ይህን ማድረግ የሚችሉ ሰዎችን አሰባስበናል፣ ስራውን ተከታተሉና ህዝቡን ተጠቃሚ እናድርግ" ሲባልም አይወዱም፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ነገሩ ተቀባይነት ባይኖረውም፣ ስልጣኑን ሳይነኩበት “እመራዋለሁ” የሚለውን ህዝብ የሚጠቅምን ሀሳብ የሚያቀርቡለትን የራሱን የዞኑን ተወላጆች የማይቀበል ማነው ቢባል የዚህ ዞን አመራሮች ናቸው ለሚለው ማስረጃ ከሚሆኑት ከብዙ አስረጂዎች ውስጥ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ የሚያውቃቸውን ተግባራዊ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ፣ ዶክተር ቦጋለች ገብሬ አዚያ አካባቢ ባደረገችው መልካም ጥረትና ትኩረት በሚስብ የበጎ አድራጎት ስራዋ ዓለም ሲያደንቃት ከተወለደችበት አካባቢ በምን ተገፍታ ወጣች? የተጀመሩት የአገልግሎት መስጫ ተቋሞችስ ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? ሩቅ ሳንሄድ እዚሁ ሀምበርቾ የሚባለው ግሩፕ እንደአቅሙ፣ "የከምባታ ጠምባሮ ሲምፖዚየም" መዘጋጀት አለበት፣ በሚል ለሶስት ዓመታት በሀምበሪቾ ግሩፕ ሲቀሰቀስና የሚቀርበውን ነገር ሁሉ ሲያደራጅ፣ በአለምአቀፍ ደረጃ ሰዎችን በማሳመን ከርሞ፣ ይህን የሚያስተባብሩ በሳል ባለሙያዎች የተዋቀሩበትን አሰራር ሁሉ ወዲያ ገፍተው፣ ድንገት ደርሰው የሰውን ራዕይ በመንጠቅ ሳያፍሩና ትንሽም ህሊናቸውን ሳይወቅሳቸው፣ ዓላማውን የማያስፈጽም የተደነባበረ ዝግጅት ላለፉት ሁለት ዓመታት "ለማካሄድ ሞክረዋል፡፡ ግን እውነት ሲምፖዚየም ዓላማው ልብስ ሰፊዎችንና የስጋ ነጋዴዎችን ማበልጸግ ነው? አነሳሱም ሆነ መሰረታዊ ዓላማው በፍጹም ይህ አልነበረም፡፡ ይህ ለምን ይሆናል ሲባሉ ደግሞ የሚደረድሩዋቸው ውሃ የማያነሱ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ዞኑን የሚጎዱ ከመሆን ወዲያ እዚህ ግቡ የማይባሉ ናቸው፡፡

የአካባቢው ከልማት የመራቅ አባዜና ከሌላው ተቀራራቢ እድገት ከነበራቸው ዞኖች ጋር ሲስተያይ ወደኋላ መቅረቱ አሳሳቢ ከመሆኑ በቀር፣ “ምንም አልተሰራም” ብሎ ለመደምደምና ጥፋቱን ሁሉ ከአመራር ጋር የተያያዘ አድርጎ ማቅረቡም ተገቢ አይሆንም፡፡ ማህበረሰቡ በባህሉ ተጽዕኖና በእምነቱ አካሄድ ችግሮችን ለመፍታት የሚያደርገው ዘገምተኛ ጥረት ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እርስ በርስ ወረዳ ከወረዳ፣ አንዱ ጎሳ ከሌላው፣ በሰፈርና በጎጥ በሚነሱ አንዳንድ የራስ ወዳድነት እንቅስቃሴዎችም ለእድገቱ አለመፍጠን እንደምክንያት ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ ከዚህም ሌላ፣ የተማረውና በተለይም በእውቀት ልቆ የሄደው ክፍል ከአካባቢው ርቆ፣ ከክልም አልፎ፣ በፌዴራልና አለም አቀፍ ደረጃዎች ተወዳድሮ በመስራት ላይ ማተኮሩ በራሱ ገንቢ ቢሆንም አካባቢውን እንዲረሳ ማድረጉ ግን የማይካድ ነው፡፡

በዚህም ተባለ በዚያ ችግሮቹን ለመፍታት፣ ብሎም ከመንግስት በሚገኘውም ሆነ በአካባቢው ተነሳሽነት ሊሟሉ የሚችሉትን ሁኔታዎች የማስተባበርና የመምራት ስራ በአመራሩ ላይ የሚወድቅ በመሆኑ ይህንኑ የማጠናከርና የማሟላት ስራ ቢሰራ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያምናል፡፡ ባብዛኛውእዚህ የምንወያየው የአካባቢው በልማት ወደኋላ መቅረትን በሚመለከትና “በመንግስት በኩል ሊደረግ ይገባዋል” ብለን ስለምናስበው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን፣ “ችግሮቹ ሁሉ የመንግስት ናቸው፣ ይህም የሚፈታው በመንግስት ብቻ ነው፣ ያ ካልሆነ ደግሞ እንደዚህ ወይም እንደዚያ እንሆናለን ወይም እናደርጋለን” የሚሉት አንዳንድ አባባሎች ያልበሰሉና እንጭጭ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ የማህበረሰቡን ባህል ካለማወቅም ሌላ ግብታዊና ሰላማዊ አብሮ የመስራትና የማደግን ይሁንታ የማያሳዩም ናቸው፡፡

ችግሮች እንዳሉና አካባቢው ትኩረት እንደተነፈገው ማሳሰቡ ተገቢና ህጋዊ ነው፡፡ መፍትሄውም እንደዛው ተመክሮና ተዘክሮ ከሌሎች የአካባቢውና የአገሪቱ እቅዶች ጋር ተስተያይቶ፣ የኛንም ትብብረ ባገናዘበ መልኩ እንደሚመጣ፤ ለዚህም በአካባቢው የተመረጡት ሰዎች ያለባቸውን የማድመጥና ህዝቡን የማስተባበር ችግር አስተካክለው አብረን እንድንሰራና አከባቢያችን እንድናለማ መንገዱን ሊያመቻቹልን ይገባል፡፡ የፌዴራሉም ሆነ የክልሉ መንግስትም ባንጻሩ ከሌሎች የሀገሪቱ ማህበረሰቦች በተጓዳኝ ተመጣጣኝ የሆነ የአገሪቱን ሀብት የማከፋፈል ሃላፊነቱን እንዲወጣ አበክረን እንጠይቃለን፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ ባንድ ሳምንት ዩኒቨርሲቲ ይገንባና ይደር ወይም ደግሞ የጨውና የሲሚንቶ ፋብሪካ ዛሬ መገንባት ይጀምር የሚል ህልም የለንም፡፡ ይሁን እንጂ ሊገነባ የሚገባው ነገር መጠናችንንና አስተዋጽዖዋችንን ባገናዘበ መልኩ ተመጣጥኖ እንዲደረግልን፣ ይህም በተጨባጭ እንዲረጋገጥልን እንጠብቃለን፡፡ ሁሉም በስርዓቱ ሲሄድ በስርዓቱ የልማት ተጠቃሚ መሆን ካለብን መብታችን ሊከበር ይገባል ብሎ መጠየቅ አያሳፍረንም፡፡ መስፈርቶች ስርጭትን ለማደላደል መመዘኛ መሆናቸው ባይካድም፣ “አንድን አካባቢ ደጋግመው እንዲጎዱ የሚዘጋጁ እስኪመስሉ ጉንጭ አልፋ በሆነ ምክንያትና ስሌት በጠረባ ስንመታ ዘመናት መቁጠር የለብንም” የምንል ብዙዎች ነን፡፡ለእኛ አካባቢ መሰረተ ልማት ሲሆን በክልሉም ሆነ በመሪ ድርጅቱ የሚቀርቡት ተጨማሪ የሚመስሉ መስፈርቶች አካባቢው እንዳያድግ ታልመው የተቀመጡ እስኪመስሉ ማነቆነታቸው አሳስቦናል፡፡

በዚህ አጋጣሚ፣ የአካባቢውን ወጣቶች ቀና አስተሳሰብና የዋህ የልማት ፍላጎት ለሌላ ዓላማ እንደሆነ አድርገው ለመተርጎም ደፋ ቀና የሚሉ፣ ለአካባቢው እድገት የህዝቡን ሀሳብ ይዘው ከመከራከርና ለልማት ከማነሳሳት ይልቅ መንግስትን ከህዝቡ ለማጋጨት ቀዳዳ ለሚፈልጉ ጥቂት ካድሬዎች አዚህ ጋር አንድ ነገር ማሳሰቡ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን የሰሞኑን የልማት ጥያቄ፣ “የጥቂቶች ጸረ ልማቶች ቅስቀሳ ነው” እያሉ (ልማት በሌለበት) ስንፍናን ለመሸፈን የሚደረግ ሩጫ በመሬት ላይ ያለውን የገጠጠ እውነት በጭራሽ እንደማይሸፍነው

ሊረዱትና ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ የዞኑ ህዝብ ጥያቄ የሁሉም እንጂ የአንድ አካባቢ፣ የአንድ ወረዳ ወይም የፖለቲካ ጥያቄ አይደለም፡፡ የልማት ጥያቄን የሚጠላ ያለ ይመስል ህዝቡን ለመከፋፈልና መልሶ ለማስጠቃት፣ ጥያቄውም ተጠንቶ እነዳይመለስ ለማለባበስ መሞከር ፋይዳ ቢስነት ሲሆን ህዝቡም ሁሉን እየታዘበ መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል፡፡

ለጠላትም ሆነ ለወዳጅ ሊያውቀው የሚገባው ነገር ቢኖር፣ የከምባታም ሆነ የጠምባሮ ህዝብ በታሪኩም ሆነ በልማዱ መብቱን ለማስከበርም ሆነ ለመጠየቅ ህጋዊ የሆነ መንገድ ተከትሎ፣ ግዴታውን እየተወጣ፣ ጠንክሮ እየሰራና በእምነቱ መሰረት ነገሩን ሁሉ ለአምላኩ እየተወና ጠላቶቹን ሁሉ ሳይቀር በመውደድና አብሮ በመኖር እያስደነቀ በበረከትና በተኣምራት የሚኖር ህዝብ ነው፡፡ አብዛኞቻችን ይህን ታሪኩን እናውቃለን፤ ከዚህ ጠንካራ የባህል እሴቱ ደግሞ አዎንታዊ የሆነው ባሁኑ ትውልድም የበለጠ እንዲዳብር እንጥራለን እንጂ ጠቃሚና ጎጂውን ሳናስተያይ በመጣው ንፋስ ሁሉ አንወሰድም፡፡

መንግስትንና ህግን እናከብራለን፤ መሪን እናከብራለን፡፡ መፍትሄዎችን በውይይትና ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ በእምነታችንና ከትምህርት ባገኘነው የዳበረ ስነምግባር በማፈላለግ ችግሮች የሚፈቱበትን መንገድ ከዚህ ቀደም እንደምናደርገው አሁንም እንቀጥላለን፡፡ የአካባቢው ህዝብ የጠየቀውን ሰላማዊ የልማት ጥያቄ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ለመምራት የሚፈልጉ አንዳንድ ሰዎች፣ አሳሳች ፕሮፓጋንዳ በማስተጋባት ከውይይት መድረክ ይልቅ ለሌላ አማራጭ ህዝቡን ለመቀስቀስ ማነፍነፋቸውን እያየን ከመሆኑም በላይ መንግስትም በመፍትሄው ረገድ ምላሹን ግልጽ ባለማድረጉ ማህበረሰቡን መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደቆመ አድርገው እየሳሉት ነው፡፡ "በሀምበሪቾ ዙሪያ" ይህን በተመለከተ በብሎጉም ሆነ በፌስ ቡክ ገጹ ሰላማዊ መንገድን ያልተከተለ ሀሳብን እንደማያሰራጭ ያለውን መርህ ብቻ ሳይሆን የመከላከልም ሀላፊነት እንዳለበት ስለሚገነዘብ የተቻለውን ሁሉ ጥረት ያደርጋል፡፡ዳለው፣ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዳለው፣ "ጨለማን ጨለማ አይገልጠውም፤ ብርሃን እንጂ፡፡"

በመጠረሻም፣ ሁላችንም ለአካባቢያችን ልማትም ሆነ ለአገራችን እድገት በጋራ ሃላፊነት ያለብን እንደመሆኑ ተጋግዘን፣ መንግስትንና ህግን አክብረን ሃሳባችንን ብናካፍል ለሁሉም ሊያግዝና ትምህርትም ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ሀሳባቸውን በቀናነት የሚያካፍሉ ሁሉ ይበረታታሉ፡፡

ዓይነታችን የተለያየ ነው፤ በውይይት የማይፈታ ነገር ግን የለም፡፡ (መንቾ ከም)

(Haagarunne holamaa, ikkodaa hasaawwu dorumburru yobaa! - Mancho Kam)